የሪል ስቴት ገበያው እንዲሰክን አድርጓል!
የሪል ስቴት ገበያው እንዲሰክን አድርጓል!
#Ethiopia | የአዲስ አበባ ከተማ ሪል ስቴት ገበያ በዋጋ ደረጃ ለመስከኑ የኦቪድ ግሩፕ አስተዋፅዎ ቀላል አይደለም ። ኦቪድ ግሩፕ በሪል ስቴት ልማት ክንፉ ፣ የገነባቸው ቤቶችን በብዛት ለገበያ ማቅረቡ የሪል ስቴት ገበያው እንዲሰክን አድርጓል - ወይም ሰብሯል ።
ቀደም ባሉት ወራት በዋጋ ሽቅብ ይጎን የነበረው የሪል ስቴት ገበያ የዋጋ ቅናሽ እየታየበት ነው - ዋጋውን ጣሪያ የሰቀሉ ጭራሽኑ ጠያቂ አጥተዋል ።
ግዙፉ የሪል ስቴት ዘርፍ ዘገር ነቅናቂ ሆኖ የቀረበው ኦቪድ - በታሪክ ተመዝግቧል ...... ብራቮ ዮናስ ታደሰ !
በአዲስ አበባ ከተማ የሪል ስቴት የካሬ ሜትር ዋጋ ወቅታዊ ነፀብራቅ ምን መልክ ይዟል ተብሎ ቢታይ - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ባስጠናው ጥናት የአንድ ካሬ ሜትር የሪል ስቴት መገንቢያ ዋጋ ከ 30,000 ብር እስከ 40,000 ብር - አለፍ ብሎም እስከ 50,000 ብር ነው ።
ነገር ግን ይህንን ዋጋ ብዙዎቹ የሪልስቴት አልሚዎች በፍፁም አይቀበሉትም ። ይልቁኑ እንደየ ሪልስቴት ግንባታው ደረጃ የሚለያይ ቢሆንም በአልሚዎች ጥናት የሪል ስቴት የግንባታ ዋጋ በካሬ ሜትር ከ 63,000 ብር እስከ 70,000 ብር ይደርሳል።
የሪል ስቴት መገንቢያ ቦታ በሁለት መንገድ ይገኛል ። አንድም ከአስተዳደሩ ሁለትም ከግለሰቦች በግዥ ። ከግለሰቦች በግዥ የሚገኘው ውድ እንደመሆኑ በግንባታው ላይ የመሬት ዋጋ ፣ የሠራተኛ እና የመሳሰሉ ወጪዎች ሲጨመሩበት ዋጋውን ማናሩ አይቀርም ።
ኦቪድ ግሩፕ ገበያውን ከመቀላቀሉ በፊት አብዛኛዎቹ አልሚዎች ለገበያ ያቀረቡትን ሪል ስቴት በካሬ ከ 80,000 ብር እስከ 120,000 ብር ይጠሩ ነበር - በውጭ ምንዛሪ ደግሞ በካሬ ሜትር ከ 3,000 እስከ 4,000 ዶላር ድረስ ይጠራሉ - ከዚህም በላይ ዋጋ የሚጠራላቸው ቅንጡ ሪልስቴቶች እዚህም እዚያም እንዳሉ አሉ!
በአሁኑ ገበያ ግን በካሬ ሜትር 70,000 ብር እና ዙሪያውን ፣ በውጭ ምንዛሪም 2,000 እና ዙሪያውን እየተጠራ ይገኛል ። ከዚህ ባለፈም ከ10 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ማማለያ እየተሰጠ ነው ።
በዚህ መሀል ማን ሰንጥቆ መጣ !? ለሦስት አስርት ከግንባታ ተገልሎ የቆየው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በለውጡ ዳግም አንሰራራ - ረሻድ ከማል የሚባል ዶዘር መጣለት - ፌቤኮ ተገማች ባልሆነ መንገድ በዋና ዋና ግንባር ቦታዎች ሁነኛ ህንፃዎችን ገንብቶ ባልተጠበቀ ዋጋ ቤቶችን ገንብቶ ለገበያ ሲያቀርብ - ገበያው ከኢኮኖሚ ማንሰራሪያ ባሻገር ለብዙሃኑ ሃብት ሆነ ...
ግን ግን የግልና መንግስት አጋርነት ( PPP ) ከመንግስት በ 70/30 ቀመር መሬት የወሰዱ ሪል ስቴት አልሚዎች በስንት ብር ቢሸጡት ያዋጣቸው ይሆን !?
በ70 ሽህ ? መንግስት ከተገነባው ሪል ስቴት ድርሻውን ሲወስድ አልሚዎቹ የመገንቢያ ዋጋውን እንዴት አብቃቅተው አትራፊ ይሆኑ ይሆን - ልናይ ኋላ!
በልዩ ሁኔታ የሚታይ ቢሆንም የፐርፐዝ ብላክ ዋጋ ሳያስደምም የሚቀር አይደለም - የፐርፐዝ ብላክ ነገር እስካሁን መጨረሻው ባይለይም አምስት ቢሊየን ብር ቦታ ገዝቶ ፤ በ 60 ቢሊዮን ብር 113 ወለል ህንፃ ከነ አጀቡ ገንብቶ - ከአክሲዮን ድርሻ ጋር ፣ መቶ ካሬ ሜትር ቤት በ 1.5 ሚሊዮን ብር ፤ ቆየት ብሎም በ3.5 ሚሊዮን ብር ሂሳብ ( በካሬ ሜትር 15,000 ብር እና 35,000 ብር መሆኑ ነው ) መዋዋሉ ከትርፋማነት ቀመር ውጭ ነው ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሪል ስቴት ዘርፍ ለመኖሪያ ፈላጊው ጥሩ አማራጭ ገበያ እንዲሆን ካስፈለገ የመሬት አቅርቦት ፣ የፋይናንስ አማራጭ ፣ የሸማች መብት ጥበቃ ወሳኝነት አላቸው - በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቢሊየነሮች የገቡበት ዘርፍ መሆኑ ልብ ይሏል - የዚያኑ ያህልም የተካኑ ባለካልኩሌተሮችም ዘርፉን ተቀላቅለዋልና መፍዘዝ ጥሩ አይደለም !
ውድነህ ዘነበ
Comments
Post a Comment