የቤት ዋጋ እንዴት ሊቀንስ ይችላል?

 የቤት ዋጋ እንዴት ሊቀንስ ይችላል?

*****

"ቤት አትግዙ " የሚል የሶሻል ሚዲያ ቻሌንጅ የማከብረው ወዳጄ ልኮልኝ ተመለከትኩ።
አላማው በደምሳሳው ቤት ውድ ስለሆነ እስኪቀንስ ድረስ አትግዙ የሚል ነው...ይሄ ብዙም ውጤታማ ሊሆን የማይችል ቻሌንጅ እንደሆነ ቢታወቅም ሀሳቡ ግን የሚበረታታ  አይደለም ምክንያቱም ስሁት ነው።

የሪል እስቴት ዘርፍን በቅጡ ካለመገንዘብ የመጣ ቤት ተወዷል ብሎ ለውድነቱም አልሚዎችን ብቻ ተወቃሽና ተከሳሽ ለማድረግ የታሰበ የችግሩን መሰረት ያልተረዳ ነው።  እስኪ የዘርፉን አሰራርና ችግሩን እንድንረዳ ስለ ሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ዋና ተዋናዮችና አስተዋጽኦዋቸው ጥቂት እንበል። 
ሀ) ባለድርሻ አካላትና ድርሻዎቻቸው
**
የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት አምስት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት አሉት። የሀገራችንን ሁኔታ ታሳቢ አድርገን ስናቀርበው ከዚህ በታች የተገለጸውን ሊመስል ይችላል:-
፩) አልሚ (Developer) :- ስራ ፈጣሪ ነው፣ መሬትን ወደ ውጤታማ የሆነ ተፈላጊ የመኖሪያ ስፍራ በመቀየር ትርፍን የሚያገኝ መላ ፈጣሪ ነው፣ የገንዘብ አምጪ፣ የኪሳራሃላፊነት ወሳጅ፣ ቀጣሪ ሲሆን ዓላማው የገንዘብ ትርፍ ማግኘት፣ የቤት ችግር መቅረፍ ቢዝነሱ ያደረገ፣ ዘላቂ ንብረት ማፍራት፣ ጥሩ ስም መገንባት ...
፪) መንግስት(public organization):- መንግስት ዜጎች ቤት እንዲያገኙ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ያወጣል፣ ለቤት ልማት የሚሆን መሬት ያቀርባል፣ የግንባታ ሂደቱን ይከታተላል፣ የግብይት ሂደቱን ይቆጣጠራል....
በሪል እስቴት ልማት ውስጥ የመንግስት ዋና ፍላጎት  የልማቱ ሂደት በስኬት ተከናውኖ   ዜጎች ቤት እንዲያገኙ ማድረግ፣  የህዝብ ሃብት የሆነው መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ....
፫) ካፒታል ማርኬት:- ይህ ለግንባታም ሆነ ለቤት ገዢዎች ብድር የሚሆን የገንዘብ አቅርቦትን የሚያቀርቡ ባንኮችንና ሌሎች ወደፊት የሚመጡ የገንዘብ አቅርቦት የሚሰሩ ተቋማት ሲሆኑ ተሳትፏቸውም ለልማቱና ለቤት ገዢዎች ገንዘብ ማቅረብና ከልማት ሂደቱ ማትረፍ ነው። ፍላጎታቸው ኢንቨስትመንቱ አዋጭ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

፬) የቤት ገዢዎች (ተከራዮች) (ደንበኞች):- ዋና ፍላጎታቸው ለመኖር በቂ የሆነ ፣ በጊዜው ተጠናቅቆ መረከብ፣ በቂ ስፋት ያላቸው መገልገያ ክፍሎች ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት ማግኘት ሲሆን። የቤት አልሚው ይህንን የቤት ገዢዎችን አቅምና ፍላጎት በገበያ ጥናት አጥንቶ መገንባት ይጠበቅበታል።

፭) የተለያዩ ባለሙያዎች (Development Team ) :- የሪል እስቴት ዘርፍ ብዙ ሙያዎችን የሚጠቀም ዘርፍ ነው። ለምሳሌ አርክቴክቶች፣ መሃንዲሶች፣ ገንቢዎች፣ የግብይት ሂደት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች፣ የፋይናንስ፣ የባንኪንግ ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለሙያዎች፣ IT ባለሙያዎች፣ የህግ ... ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ። ባለሙያዎቹ በግልም በህብረትም በየሙያቸው ያለውን ከፍተኛና ፈጠራ የተካተተበት የደንበኞችን  ፍላጎት መሰረት ያደረገ ውጤት እንዲመጣ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው።
ለ) ቤት እንዲቀንስ የሚጠበቅባቸ አስተዋጽኦ
****
የሪል እስቴት ልማትና ግብይት የተሳካ እንዲሆን ከላይ የተዘረዘሩት ባለድርሻ አካላት የሚጠብቃቸውን ያለማጓደል ሊያበረክቱ ይገባል።
ለምሳሌ :-
፩) መንግስት ለአልሚዎች መሬት በቅናሽና በብዛት ካረበ፣  የዲዛይን ማጽደቅና ክትትል ስራውን ካሳለጠ፣ ግብይቱ የሚመራበት መመሪያና ግብይቱን የሚመራ  አካል ሰይሞ በስርዓት እንዲመራ ካደረገ፣ በርካታ ቤቶችን ለሚገነቡ አልሚዎች የግንባታ  ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ  ቢያደርግ
፪) የገንዘብ አቅራቢ ተቋማት ለአልሚዎችና ለቤት ገዢዎች በቂ የሆነ የገንዘብ አቅርቦት ቢያደርጉ
፫) ቤት ገዢዎች ጠንክረው ሰርተው ቁጠባን ባህላቸው ቢያደርጉና እቅም ቢፈጥሩ
፬) ባለሙያዎች ገበያውንና የቤት ገዢዎችን አቅምና ፍላጎት ያገናዘቡ ቤቶች የሚገነቡበትን ዲዛይን፣ ወጪ ቀናሽ የግንባታ ቴክኖሎጂ ፣ የአከፋፈል ስርዓት በጥናት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ቢያዘጋጁ
፭) አልሚዎች ዘርፉን በእውቀት በባለሙያዎች እንዲመራ ቢታደርጉ

ሐ) መውጫ በምሳሌ
**
ነገር ግን ከአምስቱ  አንዱ ሲያጎድል ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል በሌሎቹ አካላት ላይም ተጽዕኖን ያሳድራል ።
ለምሳሌ :- ባለሙያዎች ገበያውን ያላገናዘበ ውድ ቤቶች ዲዛይን ቢሰሩና ቢገነባ  ቤት ገዢዎች ሊገዙት አይችሉም፣ ካልተሸጠ ባንኮች ያበደሩት ብር በወቅቱ አይመለሰም፣ የቤት ችግርን ስለማይቀረፍ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል ከልማቱ ማግኘት የነበረበትን ገቢ ያሳጣል፣ አልሚውም ይከስራል...

ስናጠቃልለው የቤት ዋጋ ሊቀንስ የሚችለው በአልሚዎች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱት አካላት የተናበበ የጋራ ተሳትፎ ሲኖር ብቻ ነው።

Comments

Popular Posts