📌ማስጠንቀቂያ 📌 ከፈንጅ አምካኝ ቀጥሎ ከስህተት ሊማሩበት የማይቻለው የቤቶች ግብይት ነው ይባላል

 á‰ á‰…á‹ľáˆ˜ ክፍያ ቤቶችን የሚገዙ #ቤት_ገዢዎች ሊጠነቀቁባቸው የሚገቡ ጉዳዮች

*"*"*"""

በቅድመ ክፍያ በተለያየ ሁኔታ የቤት ገዢዎች በተከፋፈለና ረዘም ባለ ሁኔታ በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶችን መሸጥ (presales) የሪል እስቴት ግብይት ውስጥ አልሚዎች እንደ ፕሮጀክት ማስኬጃ የገንዘብ ምንጭ (project finance) የሚጠቀሙበት ለቤት ገዢዎችም በተራዘመ የክፍያ ሂደት ቀስ በቀስ እየከፈሉ ቤት እንዲገዙ የሚያስችል  አስቻይ የክፍያ አማራጭም ነው።

ይህ አይነት ግብይት ውስጥ አልሚዎችም ሆነ ገዢዎች ጥንቃቄን ካላደረጉ ለኪሳራ የሚዳርግ ነው።
ከአልሚዎች የተያያዘውን አቆይተነው ከቤት ጋዢዎች ጋር የተያያዘውን እንደሚመለከተው ለማቅረብ እንሞክራለን:-

1) ከፕሮጀክት መዘግየት ጋር የተያያዘ:- ፕሮጀክቶች በተለያዩ  ምክንያቶች ይዘገያሉ ። ብዙ ግብይቶች በዶላር ምንዛሪ እኩሌታ ተሰልቶ እንዲከፍሉ ስለሚደረግ ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር የገንዘብ ምንጫቸው ከሀገር ውስጥ ያደረጉ የቤት ገዢዎች ለተጨማሪ የክፍያ ወጪ  ይዳረጋሉ። ከክፍያ ባሻገር ፕሮጀክቶች በመዘግየታቸው ከፕሮግራማቸው ውጪ ለቤት ኪራይ እየከፈሉ መኖር መቀጠላቸው ከፍተኛ ጫና ይፈጥርባቸዋል።

2) የዲዛይን እና የጥራት ችግር: በቅድመ ክፍያ የሚገዙ ቤቶች ግብይት በማስታወቂያ ላይ በሚለቀቁ የማርኬቲን ምስሎች እና በወረቀት ላይ ባሉ መረጃዎች ስለሚከናወኑ በግንባታ ሂደት በሚኖር ትግበራ በሚኖር የአሰራር ችግር፣ የማጠናቀቂያ ቁሶች ደረጃ መውረድ ወይም የዲዛይን ክለሳ የተነሳ ገዢዎች የጠበቁትን ላያገኙ ይችላሉ ።

3) ከገንዘብ አቅርቦት ጋር ያሉ ተያያዥ ጉዳዮች:- የቤቶች ግብይትን አስቻይ ለማድረግ የተወሰነ ክፍያ ከባንኮች ጋር ተያይዞ እንዲከፈል ሊደረግ ይችላል። ይህም በተራዘመ ሂደት ባንኮች ለሚያወጡት የተለያዩ የወለድ ጭማሪዎች ሊዳርግ ይችላል። ደንበኞች በራሳቸው ምንጭ በሚሸፍኑት የክፍያ ሂደት ውስጥ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑና ከክፍያ መዘግየት ጋር በአልሚዎች የሚቀመጡት ቅጣቶች ከፍ ያሉና ውልን እስከማቋረጥ የሚደርሱ መሆናቸው ። ጥቂት የማይባሉ ተለምነው የገዙ የቤት ገዢዎች በክፍያ ማዘግየት ሰበብ በቅጣት ጭምር ውላቸው ተቋርጦ ገንዘባቸውም ተቆራርጦ ያውም የከፊሉበት ቤት ለሌላ ተሸጦ እንዲከፈላቸው መደረጉ አክሳሪ ይሆንባቸዋልና አስተማማኝ  የገቢ ምንጭ እንዳላቸው ሳያረጋግጡ በአነስተኛ ቅድመ ክፍያ ተታልለው እንዲገዙ አይመከርም።

4) ከአልሚዎች ብቃትና ታማኝነት ጋር በተያያዘ:- የሀገራችን የሪል እስቴት ዘርፍ ግብይት ወጥ የሆነ የግብይት መመሪያ ስለሌለ ግብይቱ በአብዛኛው በመተማማመን ላይ የተመሰረተ ስኬቱም በአልሚዎቹ አቅም ታማኝነትና ያለፈ የስኬት ታሪክና ስም ጋር የተያያዘ ነው ። የቤት ገዢዎች በቅድመ ክፍያ ቤት የመግዛት ሂደት ወስጥ ከመግባታቸው በፊት የአልሚውን ህጋዊነት፣ የፕሮጀክቱን ህጋዊነት፣ ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ፣ የአልሚውን የፋይናንስ አቅም ፣ የቀደሙ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ስምና ዝና፣ ታማኝነት ፣ ወቅታዊ የአልሚው አቅም ፣ የበፊት ደንበኞቻቸውን ምስክርነት ማድመጥ ይመከራል።
5) ከገበያ ሁኔታ ጋር በተያያዘ:- የሪል እስቴት ግብይት በቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭ (dynamic) የሚባል ሲሆን በሀገራችን እስከአሁን እንዳለው ሁሌ እያደገ የሚሄድ ግን አይደለም። ተለዋዋጭነቱ ከቤት አቅርቦት ብዛትና እጥረት ጋር ብቻ ሳይሆን ከ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ፣ በየጊዜው ከሚወጡ ፖሊሲዎች ጋርም የሚያያዝ ስለሆነ ከተራዘመ የክፍያ  አማራጭነቱ ባሻገር የክፍያውን መጠን ከኢኮኖሚ ሁኔታዎች ፣ ከገበያው አካሄድ ጋር ማገናዘብ ይፈልጋል። 

ሲጠቃለል ቤት ገዢዎች በቅድመ ክፍያ ቤት ለመግዛት ከመወሰናቸው በፊት የሩል እስቴት ግብይት ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ፣ የሚገቡበትን ውል ከህግ አማካሪ ጋር እንዲመክሩ፣ በተስማሙበት የክፍያ ሁኔታ መሰረት ሊከፍሉበት የሚችል አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዳላቸው እንዲያረግልግጡ፣ የቤት ግብይት ፋይናንስን በተመለከተ እውቀት ያላቸው የባንክ ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ፣ ሾለ አልሚዎቹ እና ፕሮጀክቱ ጥናት እንዲያደርጉ፣  ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁናታዎችን እንዲገመግሙ ይመከራል።

ከፈንጅ አምካኝ ቀጥሎ ከስህተት ሊማሩበት የማይቻለው የቤቶች ግብይት ነው ይባላል። ይህም በምክንያት ነው ። ቤት እገዛለሁ ብሎ ስህተት ውስጥ የገባና ጥሪቱን ያሟጠጠ ተመልሶ ቤት የመግዛት አቅም ማዳበሩ ከባድ ነውና በእውቀትና በጥንቃቄ እንገበያይ።

Comments