ተጠንቀቁ 🏠 ሪል እስቴት ስንገዛ *22🤔?*

 መሬት ረገጥ ሀብት ግዢ

አንዳንድ ጥንቃቄዎች።
Precautions in real estate purchase

መሬት ረገጥ ሀብትን (real estate) ስንገዛ ማሰብና መከወን ያሉብን ቴክኒካዊ ጉዳዮች በ 22 ዝርዝሮች ተቀምጠዋል።  በብዙ ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ስናረግ እንደዚህ በጥልቀት ማየት የሚኖርብን ሲሆን እነዚህ ዝርዝሮች ከ አሻሻጮቹም ሆነ ከነጋዴዎቹ እውቀት በላይ በመሆናቸው ልፋት አከል ስራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም አብዛኞቹ መሬት ረገጥ  ሀብቶች የሚሸጡት በአካል በአገር ውስጥ ለሌሉ ደንበኞች ሲሆን ባለሀብቶቹ ከማከራየት ባለፈ እንደኢንቨስትመንት ስለሚያዩአቸው እንደተዘረዘሩት የሚጨነቅ ገዢም ሆነ ገንቢ እንዲሁም ተከራይ አይገጥሙንም። (ያከራየኝ ሰው ቤቱንም አይቶት አያቅም ሲባል አልሰማችሁም)

በቅርቡ ግን ሁላችንም በሰማይ ላይ ተንጠልጥለን መኖራችን ስለማይቀር ሁሉም ቴክኒካዊ ዝርዝሮች  ሁላችንንም አንድ  በአንድ እንደሚያገቡን እሙን ነው። ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎች ለማወቅ አልሚዎችን ስንጠይቅ እንደደፋር ተቆጥረን  " ትገዛ እንደሆነ ግዛ አንተ ምን ስለሆንክ ነው የምትጠይቀው? " አይነት መልስ ልናገኝ እንደምንችል ይገመታል።

ወደዝርዝሩ

1. የአልሚ እና የገዢ ውሉን ህግ ለህግ አዋቂ ከፍሎ ማስመርመር።

2. የአልሚውን የበፊት የማልማት ዝናን መፈተሽ።

3. ከተቻለ የተገነባን  ሀብት መግዛት።

4. የተገነባም ሆነ ሊገነባ ያለ ከሆነ የቤቱን ፕላን በህንጻ ነዳፊ ማስመርመር። ( እሳት ማጥፍያ ውሀ ስርአት ፣ የእሳት አደጋ ግዜ ማንቅያ ፣ በእሳት ግዜ አደጋ ማምለጫ ደረጃ እሳትና ጭስ የመቋቋም  ስርዓት  ፣ የምግብ ማብሰያ እና መታጠብያ ቤት ሽታ ማስወገጃ ፣ በቂ ተሽከርካሪ ማቆምያ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረግያ ወዘተርፈ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።)

5. የህንጻ አስተዳደር (facility management) ተገማች ወርሀዊ ወጪ ስንት እንደሆነ መጠየቅ።

6. የመነሻ አፈር ምርመራን፣ የግንባታ ወቅት ተከታታይ የብረት እና አርማታ ምርመራ ምስክር ወረቀትን ጠይቆ ማየት።

7. የኤሌክትሪክ ገመዶችና ስርዓቶችን በባለሙያ ማስመርመር። ተጠባባቂ ሀይል አመንጪ መኖሩን እና አቅሙን መጠየቅ። ቁመተ ረጅም ህንጻ ከሆነ ስለመብረቅ መከላከያ ስርአት መጠየቅ።

8. የፍሳሽ መስመር ላይ በተጓዳኝ የሚዘረጋ የማስተንፈሻ ትቦ እና ስርዓት መኖሩን ማረጋገጥ (የፍሳሽ ሽታ ማስወገጃ ዘዴ)

9. ህንጻው የከተማ የፍሳሽ መስመር አጠገቡ መኖሩን ማጣራት (አለበለዝያ በየወቅቱ የፍሳሽ ማስመጠጫ ተሽከርካሪ አዋኪነትን መቀበል)

10. በቂ ውሀ ማከማቻ እና አቅርቦት ስርአት እንዳለው በባለሙያ ማጣራት።

11. የፍሳሽ ማስወገጃ የቁመት ትቦዎች የሚያልፉበት ድምጽ በማያሳልፍ  በተከለለ ቀዳዳ እንደሚያልፍ ማረጋገጥ። (እነዚህ ትቦዎች በድምጽ ስለሚረብሹ በየመታጠብያ ክፍሉ ተጋልጠው መገኘት የለባቸውም)

12. ለተሽከርካሪ መንገድ ቀረቤታ ካለው የድምጽ መከላከያ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ ማጣራት።

13. ለሳተላይት ርቀት ማያ (TV) ወይም ለ በይነመረብ ፕሮቶኮል ርቀትማያ (IPTV) የተዘጋጀ መስመር እንዳለው ማረጋገጥ (አለበለዝያ ሁሉም ሰው የሳተላይት ሰሀኑን ሰገነት ላይ ሰቅሎ የህንጻው መልክ እንደሚበላሽ መቀበል)

14. የተጣራ እና ያልተጣራ የሚሸጥ የቤት ስፋትን ማጣራት። (መተላለፍያ፣ ደረጃ፣ ተሽከርካሪ ማቆምያ ወዘተርፈ.... በነዚህ ስፋቶች መካተት አለመካተታቸውን ማጣራት)

15. የከፍታ ተሽከርካሪን (lift) የሰው የመጫን አቅምን፣  ብዛትን  እና ፍጥነትን ማጣራት።

16. የጥያራ  ማረፍያ (airport) በአካባቢው ካለ  ጥያራው የሚያስነሳውን አዋኪ ድምጽ ዴሲቤል በተንቀሰቃሽ ስልክ መለካት።

17. አካባቢው ከቤተእምነቶች በድምጽ ማጉልያ የሚወጡ ድምጾች እንዳሉ ማረጋገጥ።

18. የሚገዛው ቤት ዋና ዋና ክፍሎች አቅጣጫን ማወቅ። (ለምሳሌ ወደሰሜን የሚከፈት ክፍል በፍጹም ጸሀይ የማያገኝ ከመሆኑ የተነሳ በአርማታ በተሰራ ህንጻ ውስጥ ፣በአዲስአበባ ከተማ አውድ እጅግ ቀዝቃዛና የሚደብት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።)

19. የሚቻል ከሆነ አልሚው የመስኮቶች ክፍተት ላይ ትንኝ-ከላ ወንፊትን ከመስታወቶች አዳብሎ እንዲሰራ ማመላከት

20. አካባቢው በቋሚነት ከሚከሰት መጥፎ ሽታ ነጻ እንደሆነ ማረጋገጥ።

21. ልማቱ ላይ እጅግ የበዛ አባወራ እንዲኖርበት የተነደፈ ከሆነ ወደልማቱ የሚወስዱ ተመጣጣኝ ስፋት ያላቸው መጋቢ መንገዶች እንዳሉ ማረጋገጥ።

22. በመጨረሻም ባለብዙ ወለል ባለብዙ መኖርያ  የጋራ መኖርያቤት የሚሰራ ከሆነ እና እንደባህላችን በቀስታ ተቁላልተው የሚሰሩ ምግቦች የሚበስሉባቸው ማብሰያ ክፍሎች የሚኖሩ ከሆነ ማብሰያ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የሽታ ማስወገጃ ስርአት በጥልቅ መመርመር ያስፈልጋል። አንደኛ ካንዱ ቤት ወደአንዱ ቡና እና ወጥ ሽታ እንዳንቀባበል ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ ሽታዎች  ከምግብ ማብሰያ ወደመኝታ እና እንግዳ መቀበያ እንዳይገቡ ሲባል ነው።

ዳዊት በንቲ። መምህርና ህንጻ ነዳፊ።

Comments