የቤት ኪራይ አዋጅ 🏠 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 🇪🇹

 በመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች


• የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ ተፈፃሚ የሚሆነው ከአንድ ክፍል ጀምሮ ለመኖሪያ አገልግሎት የተከራየና ገንዘብ የሚከፈልበትን ማንኛውም ቤት ላይ ሲሆን በሆቴል፣ ሪዞርት፣ የእንግዳ ማረፊያ እና ሌሎች በንግድ ፈቃድ መሰረት በሚከራዩ ቤቶች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

• ስለመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል

ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ውል በፅሁፍ የሚደረግ ሆኖ በወረዳ ቤቶች አስተዳደር ፅ/ቤት መረጋገጥ እና መመዝገብ አለበት፡፡ የኪራይ ክፍያውም በባንክ ወይም በሌላ ህጋዊ በሆነ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ የሚፈፀም ይሆናል። የአከራይ እና ተከራይ ውሉን ከሰኔ 1/2016 ዓ/ም ጀምሮ  በሁሉም ወረዳዎች ፅ/ቤቱ የማረጋገጥና የመመዝገብ ስራውን ተጀምሯል፡፡ ይህ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል አከራይና ተከራይ በተፈራረሙ 30 ቀናት ውስጥ የማረጋገጥ እና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ማንኛውም ያልተረጋገጠ እና ያልተመዘገበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እንዳልተደረገ ይቆጠራል። የማረጋገጥ እና የምዝገባ ግዴታን ያለመወጣት በአከራይ ወይም በተከራይ ላይ በተቆጣጣሪው አካል እስከ ሶስት ወር የሚደርስ በውሉ ላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ ያስቀጣል፡፡

ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በፅሁፍ የተደረገ የኪራይ ውል ካልሆነ በስተቀር የመኖሪያ ቤት ኪራይ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ አይችልም። እንዲሁም ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ውል ሲገባ አከራይ ከተከራይ ላይ ሊጠይቅ የሚችለው ቅድሚያ ክፍያ ከ2 ወር የቤቱ የኪራይ ዋጋ ሊበልጥ አይችልም። በዚህ የውል ዘመን ውስጥ ተከራይን ከቤት ማስወጣትም ሆነ በአዋጁ ከሚፈቀደው አግባብ ውጭ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር አይቻልም፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ

የኪራይ ውል ላይ ያለው የቤት ኪራይ ዋጋ የቤቱ የኪራይ ዋጋ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል እንጂ አዲስ የሚወጣ የቤት ኪራይ ዋጋ አሁን ላይ የለም።

አከራይ ለነባር ተከራይ ወይም ለአዲስ ተከራይ በሚያከራየው የመኖሪያ ቤት ላይ ቀደሞ በነበረው ኪራይ ላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ በአመት አንድ ጊዜ በሰኔ ወር ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ሊወስን የሚችለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሬ መሰረት በማድረግ ብቻ ነው።

አዲስ የተገነባ ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ ለኪራይ የቀረበ የመኖሪያ ቤት በሚከራይበት ጊዜ የቤቱ የኪራይ ዋጋ በአከራይና በተከራይ ስምምነት የሚወሰን ይሆናል። ነገር ግን አከራይ ቀደም ሲል ሲከራይ የቆየ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ አዲስ ቤት ያለአገልግሎት ከስድስት ወር በላይ እንዲቀመጥ ካደረገ ቤቱ ቢከራይ ሊከፍል ይችል የነበረውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ገቢ ግብር ተሰልቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ስለሚቋረጥበት ሁኔታ

1. የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል የኪራይ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በአከራዩና ተከራዩ ስምምነት፣
2. ተከራይ ቤቱን መልቀቅ ሲፈልግ የሁለት ወር የቅድሚያ ማስታወቂያ በመስጠት
3. የአንድ ቤት ባለቤትነት በውርስ፣ በሽያጭ፣ በዕዳ ወይም በሌላ ማናቸውም ህጋዊ ምክንያት ለሌላ ወገን ከተላለፈ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው ቤቱ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ የ6 ወር ማስጠንቀቂያ ለተከራዩ በመስጠት ነው።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ያለማስጠንቀቂያ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች

1. የቤት ኪራይ በውሉ በተመለከተው የመክፈያ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ከ15 ቀን ካሳለፈ
2. ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ 7 ቀን ካሳለፈ

Comments